የታሪፍ አመዳደብ የጉምሩክ ታሪፍ ምንድን ነው? የጉምሩክ ታሪፍ ማለት ወደ ጉምሩክ ክልል በሚገቡ እና ከጉምሩክ ክልል በሚወጡ ማናቸውም ዕቃዎች ላይ የሚከፈል ቀረጥን ለመወሰን የሚያስችል የዕቃዎች የቀረጥ ማስከፈያ ምጣኔ ነው፡፡ የታሪፍ አመዳደብ ምን ማለት ነው? በዕቃዎች ላይ ሊከፈል የሚችልውን የቀረጥ ምጣኔ ለማወቅ ዕቃዎችን በኤች ኤስ (የተጣጣመ የሸቀጦች መግለጫና መለያ ስርዓት) ወይም በታሪፍ መጽሀፍ ውስጥ በየትኛው ክፍል፣ ምዕራፍ አንቀጽና ንዑስ አንቀጽ ስር እንደሚመደብ ለማወቅ የሚደረግ ስራ ነው፡፡ የታሪፍ መጽሀፍ ወይም ኤች ኤስ (የተጣጣመ የሸቀጦች መግለጫና መለያ ስርዓት)ምንድን ነው? በንግድ ወይም በሌላ ምክንያት በዓለም ላይ የሚንቀሳቀሱና የሚዘዋወሩ ዕቃዎችን በቀላሉ፣ ቴክኒካዊ በሆነ ስልት እና ወጥነት ባለዉ መንገድ ለይቶ ለማወቅ ዕቃዎችን በክፍሎች በምዕራፎች፣ በአንቀጽና በንዑስ አንቀጾች በመለየት ተጠንቶ የተዘጋጀ ስርዓትን መሰረት ያደረገ ሰነድ/መጽሀፍ ነው፡፡
የዕቃዎችን ታሪፍ እንዴት መመደብ ይቻላል?
በጉምሩክ አዋጅ 859/2006 አንቀጽ 102/3 ላይ የዓለም የጉምሩክ ድርጅት (World Customs Organization) ስለሸቀጦች አመዳደብ የሚያወጣው ሰነድ ስለዕቃዎች የታሪፍ አመዳደብ ወሳኝ ማስረጃ ተደርጎ ይወሰዳል ተብሎ ተደንግጓል፡፡ በዚህ መሰረት በአለም የጉምሩክ ድርጅት አባል ሀገራት ስምምነት የጸደቀው የተጣጣመ የዕቃዎች መግለጫና መለያ ስርዓት (Harmonized Commodity Description and Coding System) በኢትዮጵያ ለእቃዎች ታሪፍ አመዳደብ ጥቅም ላይ ይውላል ማለት ነው፡፡
በአለማችን ከሚገኙ እቃዎች ከ 95 በመቶ በላይ የሚሆኑ ዝርዝርን ከላይ በተገለጸው አግባብ ስልታዊና ወጥ በሆነ አግባብ ለይቶ ለማወቅ ይቻል ዘንድ እቃዎቹ በታሪፍ መጽሀፍ ውስጥ በክፍሎች፣ በምዕራፎች፣ በአንቀጽና በንዑስ አንቀጽ ተደራጅተው ይገኛሉ፡፡ በዚህ መሰረት በታሪፍ መጽሀፍ የተለያዩ ዕቃዎች በሚከተለው አግባብ ተዘርዝረውና ተደራጅተው ይገኛሉ፡፡
- በታሪፍ መጽሀፍ ዉስጥ 21 ክፍሎች/Sections/ አሉ፤
- እነዚህ ክፍሎች በተለያየ ብዛት እና ደረጃ 97 ምዕራፎችን/Chapters/ በስራቸዉ ይዘዋል፤
- እነዚህ ምዕራፎች በተለያየ ብዛት እና ደረጃ 1222 አንቀጾችን/Headings/ በስራቸዉ ይዘዋል፤
- እነዚህ አንቀጾች በተለያየ ብዛት እና ደረጃ 5387 ንዑስ አንቀጾች/Sub-Headings/ በስራቸዉ ይዘዋል፤

በደንበኞች ትምህርትና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት
በደንበኞች ትምህርት ቡድን ለግንዛቤ ማስጨበጫ የተዘጋጀ

Today 2 Yesterday 21 Week 23 Month 201 All 8532

Currently are 33 guests and no members online