የሸቀጦች አመዳደብ ደንብ
General Rules of Interpretation (GIR)
ምንጭ፡- የ2012 ዕትም የጉምሩክ የታሪፍ ደንብ/መጽሀፍ
ትክክለኛ የዕቃዎች አመዳደብ ሥርዓትን መተግበር የሚቻለዉ በስምምነት የጸደቁትን ደንቦች በአግባቡ በመተግበር ነዉ። ደንቦቹ በቁጥር 6 ናቸው። ከደንብ ቁጥር 1 እስከ ደንብ ቁጥር 4 ድረስ ያሉት ስንጠቀማቸዉ በቅደም ተከተላቸው መሰረት ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በታሪፍ መጽሃፍ ውስጥ የእቃዎች አመዳደብ ቀጥሎ የተመለከቱትን መሰረታዊ ደንቦች በመከተል ይፈጸማል፡-

ደንብ ቁጥር አንድ (1)

ይህ ደንብ የሚያዘው የክፍሎች፣ የምዕራፎችና የንዑሳን ምዕራፎች አርዕስት ለጉዳዮቹ ማጣቀሻ እንዲያመች ብቻ የተመላከቱ ሲሆን ለሕጋዊ ሁኔታዎች ሲባል አመዳደቡ በአንቀጾችና በማናቸውም ተዛማጅ የክፍል ወይም የምዕራፍ መግለጫዎችና እነዚህ አንቀጾች ወይም መግለጫዎች በሌላ አኳኋን እንዲወሰን ካላደረጉ በቀር በሚከተሉት ደንቦች መሠረት ይፈፀማል፡-
በመሆኑም እቃዎች ሊመደቡ የሚገባቸዉ በታሪፍ አንቀጹ የእቃ አይነት መግለጫ /Terms of the heading/ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ አንቀፆቹን ወይም እቃዉን በተመለከተ የተደነገጉ የክፍልና፣ የምዕራፍ መግለጫዎች በሌላ ሁኔታ የእቃዉ አመዳደብ እንዲወሰን የማያዙ መሆናቸዉን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡
የዕቃው አይነት መግለጫ፣ የአንቀጽ፣ የክፍልና የምዕራፍ መግለጫዎች የእቃዉን ታሪፍ አመዳደብ ለመወሰን የማያስችሉ በሚሆኑበት ጊዜ የእቃዉ ታሪፍ አመዳደብ ከደንብ ቁጥር 2 እስከ 4 ባሉት ህጎች መሰረት የሚወሰን ይሆናል፡፡

ደንብ ቁጥር ሁለት (2)

በደንብ ቁጥር 1 ማለትም በአንቀጸች እና ተዘማጅ በሆኑ የክፍል እና የምዕራፍ መግለጫዎች በመጠቀም አንድን ዕቃ መመደብ ካልተቻለ ወደ ደንብ ቁጥር 2 እንሸጋገራለን፡፡ ይህ ደንብ ሁለት ክፍሎች አሉት፡፡ እነርሱም፡-ደንብ ቁጥር 2/ሀ/ እና 2/ለ/ ይባላሉ፡፡
የአተረጓጎም ደንብ ቁጥር 2/ሀ/፡-

በአንድ አንቀጽ ውሰጥ ስለአንድ ዕቃ ሲጠቀስ ጥቅሱ ያልተሟላውን ወይም ሥራው ያላለቀበትንም ዕቃ ይጨምራል፡፡ ሆኖም ያልተሟላው ወይም ሥራው ያላለቀለት ዕቃ በሚቀርብበት ጊዜ የተሟላውን ወይም ሥራው ያለቀለትን ዕቃ ትክክለኛ ባሕርይ /Essential Character) ይዞ መገኘት ይኖርበታል፡፡ እንዲሁም ጥቅሱ የተሟላ ወይም ሥራው ያለቀለት /ወይም በዚህ ደንብ መሠረት እንደተሟላ ወይም ሥራው እንዳለቀለት ተቆጥሮ ሊመደብ የሚችል ሆኖ ሳይገጣጠም ወይም ተፈታትቶ የመጣውንም ዕቃ ይጨምራል፡፡
የአተረጓጎም ደንብ ቁጥር 2/ለ/፡-

በአንድ አንቀጽ ውስጥ ስለ አንድ ማቴሪያል ወይም ሰብስታንስ ሲጠቀስ ጥቅሱ የዚያን ማቴሪያል ወይም ሰብስታንስ እና የሌሎች ማቴሪያሎች ወይም ሰብስታንሶች ድብልቅ ወይም ጥምር ያጠቃልላል፡፡ ከአንድ ማቴሪያል ወይም ሰብስታንስ ስለተሠሩ ዕቃዎች ሲጠቀስ ጥቅሱ ሙሉ በሙሉ ወይም በከፊል ከዚህ ማቴሪያል ወይም ሰብስታን የተሰሩትንም ዕቃዎች ያጠቃልላል፡፡
ከአንድ በበለጠ ማቴሪያል ወይም ሰብስታንስ የተሠሩ ዕቃዎች አመዳደብ በደንብ ቁጥር 3 መሠረት ይሆናል፡፡
ደንብ ቁጥር ሦስት (3)

በደንብ ቁጥር 2/ለ/ መሰረት ወይም በማናቸውም ሌላ ምክንያት ዕቃዎች በሁለት ወይም በበለጡ አንቀጾች ሊመደቡ የሚችሉ በሆኑ ጊዜ ምደባው እንደሚከተለው ይከናወናል፡- ይህ ደንብ በ3 ደረጃ የተከፋፈሉ ንዑስ ደንቦችን አሉት፡-
ደንብ ቁጥር 3/ሀ/

ዕቃዉን በአጠቃላይ ከሚገልጹ አንቀጾች ይልቅ በይበልጥ ለይቶ ለሚጠቅሰው አንቀጽ ቅድሚያ ይሰጠዋል፡፡
ሆኖም ሁለት ወይም የበለጡ አንቀጾች እያንዳንዳቸው በድብልቅ ወይም በጥምር ዕቃዎች ውስጥ ካሉት ማቴርያሎች ወይም ሰብስታንሶች ከፊሎቹን ብቻ ወይም ለችርቻሮ ሽያጭ በስብስብ ከተዘጋጁ ዕቃዎች ከፊሎቹን ብቻ የሚጠቅሱ በሆነ ጊዜ ከአንቀጾቹ አንዱ በይበልጥ አሟልቶ ወይም አስተካክሎ የሚገልጽ ቢሆን እንኳን እነዚያ አንቀጾች ዕቃዎቹን እኩል ለይተው እንደገለጹ ይቆጠራል፡፡
ደንብ ቁጥር 3/ለ/

በደንብ ቁጥር 3/ሀ/ መሰረት ሊመደቡ የማይችሉ ድብልቆች፣ የተለያየ ማቴርያሎችን የያዙ ወይም ከተለያየ ኮምፖነንቶች የተሰሩ ጥምር ዕቃዎች እና ለችርቻሮ ሽያጭ በስብስብ የተዘጋጁ ዕቃዎች ትክክለኛ ባህሪያቸውን/Essential Character/ ከሚሰጣቸው ማቴርያል ወይም ኮምፖነንት እንደተሰሩ ተቆጥረው ይመደባሉ፤ ይህም የሚሆነው ይህ መመዘኛ ተፈጻሚ ሊሆን እስከቻለ ድረስ ነው፡፡
ደንብ ቁጥር 3/ሐ/

ዕቃዎች በደንብ ቁጥር 3/ሀ/ ወይም 3/ለ/ መሰረት ሊመደቡ የማይችሉ በሆኑ ጊዜ እኩል አማራጭ ከሆኑ አንቀጾ መካከል በአቀማመጥ ቅደም ተከተል የመጨረሻ በሆነው አንቀጽ/Last in Numerical Order in the HS/ ይመደባሉ፡፡ እነዚህን የደንብ ሶስት ንዑስ የአተረጓጎም ደንቦች የምንጠቀምባቸው በቅደም ተከተላቸው መሠረት ነው፡፡
ደንብ ቁጥር አራት (4)

ከዚህ በላይ በተመለከቱት ደንቦች መሠረት ሊመደቡ የማይችሉ ዕቃዎች በይበለጥ የሚመስሉአቸው/Most Akin/ ዕቃዎች በሚመደቡበት አንቀጽ ይመደባሉ፡፡
አልፎ አልፎ ካልሆነ በስተቀር አብዛኛውን ጊዜ ይህ ደንብ አገልግሎት ላይ ሲውል አይታይም፤ አይበረታታምም!!! ምክንያቱም ከደንብ ቁጥር 1 እስከ ደንብ ቁጥር 3 ድረስ ያሉት ሁሉንም ዕቃዎች ለመመደብ የሚያስችሉ በመሆናቸው ነው፡፡
ደንብ ቁጥር አምስት (5)

ቀደም ብሎ ከተመለከቱት ደንቦች በተጨማሪ የሚከተሉት ደንቦች ለይተው በሚጠቅሳቸው ዕቃዎች ላይ ተፈጻሚ ይሆናል፡፡
ይህ የአተረጓጎም ደንብ መጠቅለያዎችና መያዣዎችን ለመመደብ የምንጠቀምበት ደንብ ነው፡፡ ደንቡ በሁለት የሚከፈል ሲሆን፤ የአተረጓጎም ደንብ ቁጥር 5/ሀ/ እና 5/ለ/ ይባላሉ፡-
ደንብ ቁጥር 5/ሀ/፡-

የካሜራ መያዣ፣ የሙዚቃ መሣሪያ ማኀደር፣ የጠመንጃ ማኀደሮች፣ የንድፍ መሣሪያ መያዣ፣ የሐብል መያዣ እና እነዚህን የመሣሰሉ መያዣዎች፤ በተለይ የተወሰኑ ዕቃዎችን ወይም የዕቃዎችን ስብስብ ለመያዣ በቅርጽ የተሠሩ ወይም የተገጠሙ፤
አገልግሎታቸው ለረዥም ጊዜ ሆኖ ከሚይዟቸው ዕቃዎች ጋር በአንድነት የሚገኙ፤ ከዕቃዎች ጋር በአንድነት የሚሸጡ ሲሆኑ ዕቃዎቹ በሚመደቡበት አንቀጽ ይመደባሉ፡፡ ሆኖም ይህ ደንብ የጠቅላላውን ዕቃ ትክክለኛ ባሕርይ በሚወሰኑ /በሚያሳዩ/ መያዣዎች ላይ ተፈጻሚ አይሆንም፡፡
እነዚህ ከላይ የተገለጹት ሁኔታዎች ካልተሟሉ መያዣው እና ዕቃው በየሚመለከታቸው የታሪፍ አንቀጽ ለየብቻ ይመደባሉ፡፡
ደንብ ቁጥር 5/ለ/፡-

ከዚህ በላይ በደንብ ቁጥር 5/ሀ/ የትመለከተው እንደተጠበቀ ሆኖ ዕቃዎችን እንደያዙ የሚቀርቡ መጠቅለያ ማቴሪያሎችና መያዣዎች በተለምዶ የዕቃዎቹ መጠቅለያ በመሆን የሚያገለግሉ ከሆኑ ከዕቃዎቹ ጋር በአንድነት ይመደባሉ፡፡ ሆኖም እንደነዚህ ያሉት መጠቅለያ ማቴሪያሎች ወይም መያዣዎች ለዚህ አገልግሎት በተደጋጋሚ ለመዋል ተስማሚነታቸው በግልጽ ከታወቀ ከዕቃዎቹ ጋር በአንድነት እንዲመደቡ ይህ ደንብ አያስገድድም፡፡
ደንብ ቁጥር ስድስት (6)

ለሕጋዊ ሁኔታዎች ሲባል በአንድ አንቀጽ ሥር ባሉት ንዑስ አንቀጾች ውስጥ የዕቃዎች አመዳደብ በንዑስ አንቀጾቹ በተመለከተውና በማናቸውም ተዛማጅ የንዑስ አንቀጽ መግለጫዎች መሠረት እና አስፈላጊ ማስተካከያ ተደርጎ ከዚህ በላይ በተመለከቱት ደንቦች መሠረት ሲሆን፣ በእኩል ደረጃ ላይ የሚገኙ ንዑስ አንቀጾችን ብቻ ማነጻጸር እንደሚቻል መታወቅ አለበት፡፡ ለዚህ ደንብ ሲባል፣ የቃሉ አገባብ በሌላ አኳኋን እንዲወሰን ካላደረገ በቀር፣ ተዛማጅ የክፍልና የምዕራፍ መግለጫዎችም ተፈጻሚ ይሆናሉ፡፡

በደንበኞች ትምህርትና ድጋፍ ዳይሬክቶሬት
በደንበኞች ትምህርት ቡድን ለግንዛቤ ማስጨበጫ የተዘጋጀ ሲሆን በህግ ፊት እንደ ማስረጃ ሊቀርብ አይችልም፡፡

Today 1 Yesterday 21 Week 22 Month 200 All 8531

Currently are 32 guests and no members online