ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የተቋማት የተቀናጀ ስራ እንደሚያስፈልግ ተገለጸ ከጊዜ ወደ ጊዜ በዓይነቱና በአፈጻጸም ስልቱ መልኩን እየቀያየረ የመጣውን ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድን ለመከላከልና ለመቆጣጠር የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት የተቀናጀ ስራ መስራት ይገባቸዋል ሲሉ በጸረ ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ መከላከል የንቅናቄ መድረክ የተሳተፉ አካላት ገልጸዋል፡፡ በአዳማ ከተማ በዛሬው እለት በተጀመረው በዚህ የንቅናቄ መድረክ ከኦሮሚያ ክልል ከሁሉም ዞኖችና ከተማ አስተዳደሮች የተውጣጡ የጸጥታ አካላት፣ ዐቃብያነ ሕግ፣ ዳኞች ፣ የፌደራል ፖሊስ አመራሮችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት የተሳተፉ ሲሆን ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከል እየተሰሩ ያሉት ስራዎች አበረታች ቢሆኑም ከችግሩ አሳሳቢነትና ስፋት አንጻር የሚመለከታቸው ተቋማት በቅንጅት መስራት እንደሚገባቸው ተጠቁሟል፡፡ የጉምሩክ ኮሚሽን ኢንተለጀንሲ ኮንትሮባንድ ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ተገኔ ደረሰ እንደገለጹት ኮሚሽኑ ብቻውን ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድና ለመከላከልና ለመቆጣጠር ስለማይችልና የብዙ ተቋማትን ሚና ስለሚጠይቅ የሚመለከታቸው አካላት ተቀናጅተውና ተናበው በኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ እንደሚገባቸው አስረድተዋል፡፡ በጉምሩክ ህግ ዙሪያ የመወያያ ጹሁፍ ያቀረቡት የፍትሐቤር ቡድን አስተባባሪ አቶ ሀብታሙ ጥላሁን ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ አሁን ካለበት አሳሳቢ ደረጃ ለመቀነስና በሀገር ላይ የሚያመጣው ዘርፈ ብዙ አደጋ ለመከላከል ጠንካራ የመረጃ ለውውጥና አፋጣኝ የሆነ የፍትህ አሰጣጥ ሊኖር እንደሚገባ ጠቁመዋል፡፡ ኮንትሮባንድና ህገወጥ ንግድ የሀገር ኢኮኖሚ እንዲቀጭጭ ከሚያሳድረው ተጽእኖ በተጨማሪ በዜጎች ጤንነት ላይ እንዲሁም በሀገር ደህንነት የሚያስከትለው ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ያነሱት አቶ ሀብታሙ የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት እያንዳንዱ ተቋም የሚጠበቅበትን የተናጠልና የጋራ ኃላፊነት መወጣት አለበት ብለዋል፡፡ የታክስ ወንጀሎችን ለመከላከል የጸጥታ አካላት ሚናን በተመለከተ ጹሑፍ ያቀረቡት በገቢዎች ሚኒስቴር የታከስ ማጭበርበርና ምርመራ ዳሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ሲሳይ ገዙ ለታክስ አስተዳደሩ ተግዳሮት በሆኑት ታክስ ማጭበርበርና ስወራ ላይ ማብራሪያ ያቀረቡ ሲሆን የፍትሕ አካላት ታክስ ላይ የሚፈጸሙ ወንጀሎችን ልዩ ትኩረት በመስጠትና ህግን በማስከበር ስራው አጋር እንዲሆኑ ጠይቀዋል፡ በህገወጥ ንግድ ላይ የተሰማሩ ግለሰቦች የፍትህ አሰጣጥ መጓተት፣ የማስረጃ እጥረት፣ የሚመለከታቸው አካላት ኃላፊነታቸውን በአግባቡ አለመወጣት እና የአገልግሎት አሰጣጥ በሚጠበቀው ደረጃ አለመዘመን ህገወጥ ንግድና ኮንትሮባንድን ለመከላከል ያጋጠሙ ችግሮች መሆናቸው በመደረኩ የተነሱ ሲሆን ከተሳታፊዎች የተሰነዘሩትን አስተያየቶችና ጥያቄዎች በሚመለከታቸው የስራ ኃላፊዎች ምላሽ ተሰጥቶበታል፡፡

Today 0 Yesterday 21 Week 21 Month 199 All 8530

Currently are 34 guests and no members online