የጉምሩክ ኮሚሽን በሰሜን ወሎ ዞን ሰብአዊ ድጋፍ ለሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች 30 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ምግብ ነክ ቁሳቁስ እና የተለያዩ አልባሳቶችን ድጋፍ አድርጓል፡፡ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት ንግግር ያደረጉት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ ደበሌ ቃበታ፣ ኮሚሽኑ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ በተፈጥሮ እና በሰው ሰራሽ አደጋዎች ጉዳት ለደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች የገንዘብ እና የዓይነት ድጋፍ በማድረግ ማህበራዊ ኃላፊነቱን እየተወጣ እንደሚገኝ ገልጸዋል፡፡ ኮሚሽኑ በሁሉም ክልሎች ለሚገኙ እና ድጋፍ ለሚሹ ወገኖች በተቻለው አቅም ተደራሽ ለመሆን ጥረት እያደረገ መሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነር ደበሌ፣ ከለውጡ ወዲህም ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ከአራት ቢሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያላቸውን ቁሳቁስ ድጋፍ ማድረጉን አስታውሰዋል፡፡ ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታን ጨምሮ የተለያዩ ሚኒስትር መስሪያ ቤት ከፍተኛ አመራሮች በወልድያ ከተማ ተገኝተው ድጋፉን ያስረከቡ ሲሆን ሲሆን 30 ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ብር የሚያወጡ፤ 500 ኩንታል የስንዴ ዱቄት፣ የምግብ ዘይት፣ ሩዝ ፣ፓስታና ሌሎች ምግብ ነክ ቁሳቁሶች እና አልባሳት ለዞኑ አስረክበዋል፡፡ ድጋፉን የተረከቡት የሰሜን ወሎ አስተዳዳሪ ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል በበኩላቸው፣ ለዞኑ የተደረገው ድጋፍ ኮሚሽኑ እውነተኛ የህዝብ ተቋም መሆኑን ያስመሰከረበት ተግባር መሆኑን ገልጸው ድጋፉ ለተጎጅዎች በወቅቱ እና በትክክል እንዲደርስ ጥረት እናደርጋለን ብለዋል፡፡ በድጋፍ ርክክቡ ወቅት የገቢዎች ሚኒስቴር ሚኒስትር አቶ ላቀ አያሌው፣ የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ፣ የገንዘብ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታ ዶ/ር እዮብ ተካልኝ እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት፣ የፕላን በጀት እና ፋይናንስ ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ የተከበሩ አቶ ደሳለኝ ወዳጆ ተገኝተዋል፡፡

Today 5 Yesterday 6 Week 51 Month 260 All 11841

Currently are 23 guests and no members online