የኢትዮጵያ ማህጸን ጀግኖችን ከመውለድ ነጥፎ አያውቅም፡፡ በየዘመኑ ህዝብን ከጥፋት፤ ሀገርን ከመበተን ያዳኑ አያሌ ጀግኖች በሁሉም የትግል አውድማ ተፈጥረዋል፡፡ በተለያዩ የጦርነት አውደውጊያዎች ፣በህክምናው ዓለም፣ በፖለቲካው መስክ፣ በኢኮኖሚው ግንባር እና በሌሎችም መስኮች ሀገራችን ስመ ገናና ሆና ታፍራ እና ተከብራ እንድትኖር ያደረጉ አያሌ ታሪክ ሰሪዎች ነበሯት፣ ዛሬም እንዲሁ፡፡ ዛሬም በእኛ ዘመን አሸባሪው እና ዘራፊው የህዋሃት ቡድን ኢትዮጵያን ለማፍረስ የከፈተውን ጦርነት ለመመከት እየተደረገ ባለው ትግል ጠላትን ድባቅ የሚመቱ የጦር ጀግናዎች ብቻ ሳይሆኑ፣ በሌሎችም የሙያዎች ፈርጆችም በርካታ ጀግኖች ተፈጥረዋል፡፡ የሰሜን ወሎ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብጹእ አቡነ ኤርምያስም በአሁኑ ትውልድ እንደ አጥቢያ ኮከብ እያበሩ፣ ህዝብን ከጨለማ ወደ ብርሀን እየመሩ አስቸጋሪዎቹን የመከራ ቀናት ማሻገር የቻሉ ታላቅ አባት ሆነው ተገኝተዋል፡፡ ብጹእነታቸው፣ምትክ በሌላት በነፍሳቸው ተወራርደው ህይወትን አትርፈዋል ፣ የኃይማኖት ልዩነት ሳይገድባቸው ለሁሉም የልግስና እጃቸውን ዘርግተዋል፡፡ ስለሆነም ለእኒህ ሰው በሌለ ቀን ሰው ሁነው ለተገኙት፣ የልዩነት አጥር ሳይገድባቸው ውለታ ለሰሩልን የዘመናችንን ጀግና ማክበር እና እውቅና መስጠትም ተገቢ ነው፡፡ አሸባሪው የህዋሃት ቡድን በወልድያ ከተማ በቆየባቸው ቀናት የግለሰብ ቤትን ጨምሮ መንግስታዊ ተቋማትን ዘርፏል ፣አውድሟልም፡፡ ትንሽ እፍረት እና ርህራሄ ያልፈጠረበት አሸባሪው ህዋሃትም እንደለመደው የብጹእ አቡነ ኤርምያስን ተሽከርካሪ መዝረፉ የቅርብ ጊዜ ትዝታችን ነው፡፡ ይህንን ከግምት ውስጥ በማስገባት የጉምሩክ ኮሚሽንም 6.7 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ ተሽከርካሪ ለብጹእ አቡነ ኤርምያስ በስጦታ አበርክቷል፡፡ በድጋፍ ርክክቡ ንግግር ያደረጉት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ፣ አቡነ ኤርምያስ የሰሩት ታላቅ ገድል ራስን ለህዝብ መስጠት ክብርን የሚያጎናጽፍ መሆኑን ያስመሰከረ ተግባር ነው ብለዋል፡፡ ውለታቸውንም ሀገር የማትረሳው፤ትውልድም የማይዘጋው መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ድጋፉን የተረከቡት ብጹእ አቡነ ኤርምያስም፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋናቸውን አቅርበዋል፡፡

Today 5 Yesterday 6 Week 51 Month 260 All 11841

Currently are 11 guests and no members online