Asset Publisher

null “በአህጉር ደረጃ የተሰጠን እውቅናና ሽልማት በየደረጃው የሚገኙ የጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች እና ሰራተኞች ባደረጉት ጥረት እና ባስመዘገቡት ድምር ውጤት የተገኘ ነው” ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር

የአፍሪካ ምርጥ የመንግስታዊ አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ሽልማት አዘጋጅ ድርጅት አማካኝነት በተዘጋጀው አህጉር አቀፍ ልዩ ሽልማት “ምርጥ የአፍሪካ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር” ሆነው እውቅና ያገኙት የጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር ደበሌ ቃበታ ፤ ወደቢሯቸው ሲመለሱ የኮሚሽኑ ከፍተኛ አመራሮች እና ሰራተኞች ደማቅ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡

በተዘጋጀው  መርሀግብር ማጠቃለያ ላይ ንግግር ያደረጉት ኮሚሽነር ደበሌ፣ የጉምሩክ ኮሚሽን የነበረበትን ውስብስብ ችግሮች በመቅረፍ  ባለፉት አራት ዓመታት  ህዝብን እና ሀገርን ተጠቃሚ ያደረጉ በርካታ ስራዎች መሰራታቸውን አስረድተዋል፡፡

እነዚህ ስኬቶች የመጡት በምኞት ሳይሆን ጠንክሮ በመስራት የተገኙ ውጤቶች መሆናቸውን ያስታወሱት ኮሚሽነር ደበሌ፣ ኮሚሽኑ በቀጣይም  ሁለንተናዊ ለውጥ ማምጣት የሚያስችሉ ስራዎች ላይ  ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ጠቅሰዋል፡፡

“በሀገር  እና በአህጉር አቀፍ ደረጃ እየተሰጡን ያሉት ሽልማቶች ጉምሩክ ኮሚሽን በለውጥ ጎዳና ላይ መሆኑን ማሳያ ናቸው” ያሉት ኮሚሽነሩ  ሰሞኑን የተገኘው  እውቅናና ሽልማት በየደረጃው የሚገኙ የጉምሩክ ኮሚሽን አመራሮች  እና ሰራተኞች ባደረጉት ጥረት እና ባስመዘገቡት ድምር  ውጤት የመጣ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ከእውቅናና ሽልማት ባሻገር የጉምሩክ ኮሚሽን መላው ኢትዮጵያዊያን የሚኮሩበት እና እምነት የሚጥሉበት ጠንካራ የህዝብ ተቋም እንዲሆን ብርቱ ጥረት ይደረጋልም ብለዋል፡፡

የኮሚሽኑ አመራሮች እና ሰራተኞች በበኩላቸው የተሰጠው እውቅናና ሽልማት በህዝብ እና በመንግስት የተሰጣቸውን ኃላፊነት  በላቀ ደረጃ ለመወጣት ተጨማሪ አቅም እንደሚሆናቸው አስረድተዋል፡፡

በመጨረሻም የኮሚሽኑ አመራሮች እና ሰራተኞች በጋና ዋና ከተማ አክራ “ምርጥ የአፍሪካ ጉምሩክ ኮሚሽን ኮሚሽነር” ሆነው እውቅና ላገኙት  ለኮሚሽነር  ደበሌ ቃበታ ፣ ስጦታ አበርክተውላቸዋል፡፡

ጉምሩክ ኮሚሽንን የተመለከቱ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/ecczena
በድረ ገጽ፦ www.ecc.gov.et
በቴሌግራም፦ https://t.me/EthiopiaCustomsCommission