የአዋጁ መሻሻል እና የተካተቱ ህጎች

የአዋጁ መሻሻል እና የተካተቱ ህጎች

የግብር ወይም የታክስ አከፋፈል የህዝብ እና የመንግስት ግንኙነቶች ከሚገለጽባቸው አበይት መንገዶች አንዱ ነው፡፡ የመንግስትና የህዝብ ግንኙነት የሚጠናከረው ደግሞ ገቢው በሚያመጣው ልማት ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ አስተማማኝ የገቢ ምንጭ የሚገኘው ከግለሰቦችና ከድርጅቶች በሚሰበሰብ የግብር ወይም ታክስ ገቢ ነው፡፡የግብር/የታክስ ስርዓት ከገቢ ምንጭነት ባሻገር በህብረተሰቡ ዘንድ ፍትሃዊ የሃብት ክፍፍል እንዲኖር ለማድረግ፣ የኢኮኖሚውን አቅጣጫ ለመምራት፣ ኢንቨስትመንትን ለማበረታታት እና ዕድገት እና ልማትን ለማፋጠን የሚያገለግል የፊሲካል ፖሊሲ መሳሪያ ነው፡፡በመሆኑም ዘመናዊ የግብር/ታክስ ስርዓት ግልጽ በሆነ ህግ መመራት ይጠበቅበታል፡፡ ይህም በግብር ከፋዩ ዘንድ ተቀባይነትና ተፈጻሚነት እንዲኖረው ያደርጋል፡፡ በዚህ ደግሞ የግብር/ታክስ ህግ ተፈጻሚ የሚደረገው ኢኮኖሚው እና ማህበራዊ ሁኔታዎችን ከግምት ውስጥ በማስገባት በየጊዜው እየተፈተሹ ማሻሻያ ይደረግባቸዋል፡፡

በሃገራችንም ዘመናዊ የታክስ አሰተዳደር ስርዓት ከተጀመረ ከ1934 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ የግብር ህጎች ስራ ላይ ውለዋል፡፡ እንደየወቅቱ አስገዳጅ ሁኔታዎች እና መንግስታት ይከተሉት እንደነበረው ርዕዮተ ዓለምና የኢኮኖሚ ፖሊሲ ምክንያት በግብር ህጎች ላይ በየጊዜው ማሻሻያዎች ተደርገዋል፡፡  

ከነዚህም መካከል በ1934 ዓ.ም. ስለመሬት ግብር አከፋፈል የወጣ አዋጅ ቁጥር 8/34 ከስራዎች ሁሉ ግብር እንዲከፈል በ1936 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ቁጥር 60/36 ወጥቶ ሲሰራበት ቆይቷል፡፡ በ1953 ዓ.ም. በሶስት ሰንጠረዦች የገቢ ምንጮች የተከፋፈለ እና በኢትዮጵያ ውስጥ የተገኘ ማንኛውንም ገቢ ግብር እንዲከፈልበት ያደረገ የግብር ስርዓት በአዋጅ ቁጥር 173/53 ድንጋጌ መሰረት ተፈጻሚ ሆኖ ቆይቷል፡፡

ህጐቹ ረዥም ጊዜ የቆዩ እና ወቅታዊ ሁኔታን ያላገናዘቡ በመሆናቸው ከኢኮኖሚ ዕድገት ከሚገኘው ገቢ መሰብሰብ የነበረበት ግብር ወይም ታክስ ላለመሰብሰቡ አሉታዊ ተጽዕኖ ነበራቸው፡፡ ስለዚህ መንግስት በ1990ዎቹ አጋማሽ የግብር/ታክስ ሕግ ማሻሻያ ፕሮግራም በመዘርጋት የግብር/ታክስ ሕጐች እንዲሻሻሉ አድርጓል፡፡ በፕሮግራሙ መሰረት ሥራ ላይ የዋሉ ህጎች፤ በጊዜ ሂደት አገራችን ከደረሰችበት የኢኮኖሚ ዕድገትና ዓለም ዓቀፋዊ ሁኔታዎች ጋር እንዲጣጣም የሚያደርግ አሰራር ለመዘርጋት የገቢ ግብር አዋጅ 286/94ን አውጇል፡፡

 ከ14 ዓመታት በኋላ ደግሞ የ1994ቱን የገቢ ግብር አዋጅ በማሻሻል አዋጅ ቁጥር 979/2ዐዐ8 ወጥቶ ከሐምሌ1/2008 ዓ.ም. ጀምሮ በተገኘ ገቢ ላይ ተፈጻሚ ሲደረግ በተጨማሪም የፌደራል የታክስ አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 983/2ዐዐ8 እንዲወጣም ተደርጓል፡፡ ይህም በፌደራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ከነሐሴ 14 ቀን 2008 ዓ.ም. ተፈጻሚ ሆኗል፡፡

 የታክስ ህጎችን ለማሻሻል ያስገደዱ ሁኔታዎች

 ቀደም ሲል የነበረው አዋጅ በአንዳንድ የህግ አንቀጾች በስራ አፈጻጸም ላይ ችግር ሲያስከትሉ በመቆየታቸው አንቀጾቹ ግልጽነት እንዲኖራቸው አድርጓል፡፡ የዛሬ 14 ዓመት የገንዘብ የመግዛት አቅም ዛሬ ካለው አቅም ጋር ሲነጻጸር የሰፋ ልዩነት የነበረው መሆኑ፤ በዚህም በአሁኑ አዋጅ ውስጥ በገንዘብ መልክ የተቀመጡ ማስከፈያ ምጣኔዎች እና ገቢ መጠኖች ከወቅቱ የገንዘብ መግዛት አቅም ጋር የተጣጣመ እንዲሆን ማድረግ በማስፈለጉ በስራ ላይ የነበሩት የገቢ ግብር አዋጆች ተበታትነው መገኘታቸው፣ በአዋጆቹ አለመጣጣም፣ ለአሰራር ምቹ ያለመሆን ህጎቹን ለማስፈጸም ያስቸግር የነበረ መሆኑ እንዲሁም በየራሳቸው አሰተዳደር በተለያዩ ድንጋጌዎች ሲመሩ የቆዩት የግብር ህጎች በገቢ ግብር፣ በተርን ኦቨር ታክስ፣ በኤክሳይዝ ታክስ፣ በተጨማሪ እሴት ታክስ እና በቴምብር ቀረጥ ላይ ይታዩ የነበሩ ችግሮች በታክስ አስተዳደር አዋጁ ለመቅረፍና ወጥነት ያለው የህግ አተረጓጎም ስርዓት እንዲኖር አድርጓል፡፡ ብሎም የታክስ አስተዳደር አዋጁ ግልጽነትና ተገማችነት እንዲኖረው አድርጓል፡፡ በዚህም ምክንያት ወጥ የህግ አተረጓጎም ስርዓት እንዲዘረጋ አድርጓል፡፡

ግብር ከፋዩ በአግባቡና ፍትሃዊ በሆነ መንገድ አገልግሎት እንዲያገኝ፣ የቅሬታ ምንጭ እና የመልካም አስተዳደር ችግሮችንም ለመቅረፍ እንዲያግዝ ተደርጎ ተቀርጾ ሥራ ላይ ውሏል፡፡

 ቀደም ሲል በአገራችን ግብር የሚከፈለው በአራት ሰንጠረዦች ቢሆንም በእነዚህ ሰንጠረዦች ውስጥ የማይወድቁ ገቢዎች በመኖራቸው በአዲሱ አዋጅ እነዚህ የገቢ ዓይነቶች ወደ ግብር ወይም ታክስ መረቡ እንዲካተቱ ተደርገዋል፡፡ በመሆኑም አዲሱ የገቢ ግብር አዋጅ በአምስት ሰንጠረዦች ተዋቅሮ ቀርቧል፡፡

 በአዋጁ የተካተቱ አዳዲስ ድንጋጌዎች

በገቢ ግብር እና በታክስ አሰተዳደር ማሻሻያ አዋጆች ላይ በልዩ የተካተቱት ድንጋጌዎች ለግንዛቤ ያክል በከፊል በእዲህ መልክ ቀርቧል፡፡ ክቡራን አንባቢዎቻችንም ማብራሪያው በተወሰኑ ጉዳዮች ላይ ለግንዛቤ መፍጠሪያ እንደመሆኑ መጠን የአዋጁን ሙሉ ድንጋጌ ያካተተ እንዳልሆነ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡

 ማሻሻያው ዝቅተኛ የገቢ መጠን ላይ የሚገኙ ዜጎችን ከግብር ነጻ አድርጓል፡፡ ከመቀጠር የሚገኝ የገቢ ግብር እና የኪራይ ገቢ ግብር ላይ የገቢ ማስከፈያ መጣኔው እንዳለ ሆኖ በማስከፈያ የሚወድቁ መጠኖች ማሻሻያ ተደርጎባቸዋል፡፡ በዚህም አሁን ላይ እስከ 600 መቶ ብር የወር ደመወዝ የሚያገኝ ሰው ከግብር ነጻ ሲሆን በዓመት ከ7ሺ 200 ብር በታች ዓመታዊ የኪራይ ገቢ የሚያገኝ ሰው ከኪራይ ገቢ ግብር ነጻ ሆኗል፡፡

 በዓመታዊ የሽያጭ መጠናቸው መሰረት የግብር ከፋዮች ደረጃ ማሻሻያ ተደርጎበታል፡፡ በዚህም ዓመታዊ የሽያጭመጠናቸው ከ500ሺ ብር በታች የሆኑ ግብር ከፋዮች በደረጃ “ሐ”፣ ከአንድ ሚሊየን በታች እስከ 500ሺ ብር የሆኑ ደረጃ “ለ” እና ከአንድ ሚሊየን እና ከዚያ በላይ የሆነ ደግሞ በደረጃ “ሀ” የግብር ከፋዮች ደረጃ ላይ እንዲቀመጡ አድርጓል፡፡

 በንግድ ስራ ላይ የተሰማሩ ሰዎች እንዴት የሂሳብ መዝገብ መያዝ እንዳለባቸው አዋጁ ደንግጓል፡፡ በዚህም የሂሳብ መዝገብ መያዝ ያለባቸው ሰዎች በሂሳብ መዝገብ ሪፖርት አዋጅ በተደነገገው መሰረት የዓለም አቀፉ የፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎችን ያሟላ ሲሆን ለደረጃ “ለ” ግብር ከፋዮች ቀላል የሂሳብ መዝገብ አያያዝ ዘዴን እንዲከተሉ ያደረገ ነው፡፡

 ቀደም ሲል የታክስ ሂሳብ ሥራው በአጠቃላይ ተቀባይነትን ባገኘው የሂሳብ አያያዝና አሠራር መርሆዎች (GAAP) መሠረት እንዲከናወን ይደነግግ ነበር፡፡ በእነዚህ መርሆዎችም ዙሪያ ያለው የተግባርና የግልጽነት መጓደል እንዲሁም የኦዲተሮች አቅም ማነስ በታክስ አስተዳደሩ ላይ ተጽዕኖ ፈጥሮ ቆይቷል፡፡ በአዲሱ አዋጅ ግን የታክስ ሂሳብ አሠራር ከፋይናንሻል ሂሳብ አሠራር ጋር ተጣጥሞ የሚሄድበትን ሁኔታ አመቻችቷል፡፡ ይህም በዓለም አቀፉ የፋይናንሺያል ሪፖርቲንግ ስታንዳርድ (IFRS) መሠረት እንዲመራ አድርጓል፡፡

 ግብር ከፋዩ እንደ ንግድ ስራው ዓይነት እና ባህሪ የእርጅና ቅናሽ መያዝ የሚያስችል ዘዴ ባለመኖሩ ምክንያት ቅሬታ ሲያነሳ ቆይቷል፡፡ ከዚህ ጋር ተያይዞ የሚነሱ ቅሬታዎችን ከግምት በማስገባት የእርጅና ቅናሽ ዘዴዎች በዓለም አቀፉ ፋይናንስ ሪፖርት ደረጃዎች መሰረት ተግባራዊ እንዲሆን አድርጓል፡፡ ሆኖም በሚኒስትሮች ምክር ቤት በወጣው የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/09 መሰረት ለየትኛውም የሂሳብ ዓይነት ተፈጻሚ ይሆናል፡፡

 በተለያዩ አዋጆች ላይ የሚገኘው የማዕድን እና የፔትሮሊየም ገቢ ግብር በአዋጁ መሰረት በአንድ ላይ እንዲሰበሰቡ አድርጓል፡፡ በገቢ ግብሩ መጣኔ መሰረት የተቀመጡ ተቀናሽ ወጪዎች በአዋጁ ላይ ግልጽ ሆነው በመቀመጣቸው በዘርፉ የተሰማሩትን ለማበረታታት የሚያግዝ ነው፡፡ 

 በኪሣራ ማሸጋገር መብት ላይ የተጣለው ገደብ የኩባንያው 25% አክሲዮን ለሌላ የተላለፈ እንደሆነ ኪሣራን ማሸጋገር የማይቻል ነበር፡፡ ይህም በአክሲዮን ዝውውር ላይ ተጽዕኖ ያሳድር የነበረ በመሆኑ በአዲሱ አዋጅ ገደቡ ወደ 50% ከፍ እንዲል አድርጓል፡፡

 በዓለም አቀፍ ድርጅትና የዲፕሎማሲ መብት ባላቸው ተቋማት ተቀጥረው የሚሰሩ ተቀጣሪዎች ወይም ነዋሪ ላልሆኑ ሰዎች ወይም በቋሚነት የሚሰራ ድርጅት ለሌላው ነዋሪ ያልሆነ ሰው ተቀጥሮ የሚሰራ ተቀጣሪ ከራስ ገቢ ላይ ግብሩን ቀንሶ በየሦስት ወሩ ለግብር ባለሥልጣኑ ገቢ የሚያደርግበት ግልጽ የአሰራር ስርዓት ተዘርግቷል፡፡

 በቀድሞው ዲቪደንድና የትርፍ ድርሻ ገቢ ግብር በአክሲዮን፣ በማህበር እና ሃላፊነቱ  በተወሰነ የግል ኩባንያ እንዲከፈል ገደብ የሚያደርገው አዋጅ፤ በሌሎች ድርጅቶችና ማህበር መልክ የተመሰረቱ ድርጅቶች ከትርፍ ድርሻ ግብር እንዲከፍሉ አዟል፡፡   

 የካፒታል ዋጋ ዕድገት ግብር ይከፈልባቸዋል በማለት የገለፃቸው የአክሲዮን ድርሻን ወይም ለንግድ የተያዙ ህንፃዎችን በማስተላለፍ በሚገኘው ጥቅም ላይ ብቻ ግብር እንዲከፈል ያዝ የነበረው አዋጅ ቦንድንና ሌሎች በማይንቀሳቀስ ንብረት ውስጥ የሚገኙ የድርሻ መብቶች ሲተላለፉ ግብር የሚከፈል መሆኑን አዲሱ ህግ አካቷል፡፡

 በሠንጠረዥ “መ” መሠረት ኢትዮጵያ ውስጥ ግብር የተከፈለባቸው ንብረቶች፣ መብቶች ወይም አገልግሎቶች በውጭ አገር ግብር የተከፈለባቸው ከሆነ በውጭ አገር የተከፈለን ታክስ ለማካካስ ህጉ ተፈጻሚነት እንዲኖረው አድርጓል፡፡

 በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ሰው በነዋሪነት ጽንስ ሀሳብ መሰረት ነዋሪ መሆኑን ተረጋግጦ ከኢትዮጵያ ውጪ በሚያገኘው ገቢ   ግብር መክፈል አለበት፡፡ እንዲሁም በግዛታዊ ጽንስ ሃሳብ መሰረት በኢትዮጵያ ነዋሪ ያልሆነ ሰው ከዲቪደንድ፣ ከሮያሊቲ  ወለድ፣ ከቴክኒክ እና ማኔጅመንት አገልግሎት ከሚያገኘው ክፍያ ላይ ታክስ እንዲከፈል ተደርጓል፡፡

 አዋጁ በግብር ከፋዩ የሚያዙ የሂሳብ መዝገቦች አለም አቀፉን የሂሳብ መዝገብ እንዲከተሉ ያደረገ፤ መዝገቡ መቼና በምን    መልኩ ውድቅ እንደሚሆን ግልጽ አድርጓል፡፡

 ከቅሬታ አፈታት ስርዓት ጋር ተያይዞ ግብር ከፋዩ ለሚያቀርበው ቅሬታ እውቀትና ሙያው ባላቸው ሰዎች እንዲስተናገድ እና ስራው በቋሚ የስራ ክፍል እንዲከናወን አድርጓል፡፡ ግብር ከፋዩ በስራ ክፍሉ ውሳኔ ካልተስማማ የፍሬ ግብሩን 50 በመቶ በማስያዝ ወደ ግብር ይግባኝ መሄድ ከማስቻል ባለፈ የፍሬ ግብሩን 75 በመቶ በማስያዝ ቅሬታውን ፍርድ ቤት ማቅረብ ያስችላል፡፡

 የተጨማሪ እሴት ታክስ ከተከፋይ ሒሳብ ላይ ቀንሰው ገቢ ማድረግ ሲገባቸው ይህን ተፈጻሚ ባላደረጉ የንግድ ድርጅቶች ላይ ህጉ ለባለሥልጣኑ የማሸግ ስልጣን ሰጥቶታል፡፡ 

 የግብር ወይም ታክስ ግዴታቸውን ሳይወጡ ከአገር ለመሸሽ በሚሞክሩ የውጭ ዜጎች ላይ ያለ ፍርድ ቤት ማዘዣ ትዕዛዝ ባለሥልጣኑ የ10 ቀናት የማገድ ስልጣን በህጉ ተሠጥቶታል፡፡ ይህም ለታክስ ማጭበርበር እና ስወራ በር የሚከፍቱ ችግሮችን ለመከላከል ይረዳል፡፡

.

በብዛት የተነበቡ ዜናዎች