ከ255 ሚሊዮን ብር በላይ ግምታዊ ዋጋ ያለው ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ እጽ እና ሌሎች የኮንትሮባንድ እቃዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ::
የጉምሩክ ኮሚሽን ከጥቅምት 18 ቀን እስከ 24 /2015 ዓም ባደረገው ክትትል 144 ነጥብ 8 ሚሊዮን የገቢ ኮንትሮባንድ እቃዎች እና 195 ነጥብ 1 ሚሊዮን ብር በላይ የወጭ በአጠቃላይ 339 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር የሚያወጡ ኮንትሮባንድ እቃዎች በተለያዩ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ተይዘዋል፡፡
በተጠቀሱት ቀናቶች ውስጥ 24 ነጥብ 1 እና 8 ነጥብ 2 ኪ.ግ የሚመዝን ግምታዊ ዋጋው ከ255 ሚሊዮን ብር በላይ የሆነ ካናቢስ የተባለ አደንዛዥ እጽ በአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ከሀገር ሊወጣ እና ሊገባ ሲል በቁጥጥር ስር ውሏል፡፡
ባለፉት ሰባት ቀናት የአዲስ አበባ ኤርፖርት ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽ/ቤትን ጨምሮ በቁጥጥር ስር ከዋሉት የኮንትሮባንድ እቃዎች መካከል አልባሳት፣ ነዳጅ፣ የቁም እንስሳት፣ ኤሌክትሮኒክስ፣ ቡና፣ መድሀኒት ፣ተሽከርካሪዎች፣ የመዋቢያ እቃዎች የጦር መሳሪያዎች፣ጫት፣ አደንዛዥ እጾች፣የምግብ ዘይት እና የተለያዩ ሀገር ገንዘቦች ይገኙበታል፡፡
የገቢ ኮንትሮባንድን በመቆጣጠር ረገድ ቀዳሚውን ስፍራ የሚይዙት አዲስ አበባ ኤርፖርት ፣ ጅግጅጋ ፣ እና ሞያሌ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽህፈት ቤቶች ሲሆኑ በቅደም ተከተላቸው 73 ነጥብ 4 ሚሊዮን ፣ 15 ነጥብ 9 ሚሊዮን እና 13 ነጥብ 9 ሚሊዮን ብር በላይ የሚያወጡ የኮንትሮባንድ እቃዎችን መያዝ ችለዋል ፡፡
የኮንትሮባንድ ዕቃዎቹ በጉምሩክ ኮሚሽን ሰራተኞች ፣ በፌደራል ፖሊስ፣ በክልል ፖሊስ አባላትና ህብረተሰቡ ባደረጉት የጋራ ጥረት በፍተሻ፣ በበረራና በጥቆማ የተያዙ ሲሆን የኮንትሮባንድ እቃዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ 11 ግለሰቦች እና 36 ኮንትሮባንድ ጭነው የተገኙ ተሽከርካሪዎች በቁጥጥር ስር ውለዋል፡፡
የጉምሩክ ኮሚሽን በዚህ የህግ ማስከበር ስራ ላይ ለተሳተፉ የኮሚሽኑ ሰራተኞች ፣ የክልልና የፌደራል ፖሊስ አባላት እንዲሁም ለመላው ህዝባችን ምስጋናውን ያደርሳል፡፡
የኮንትሮባንድ እና ህገወጥ ንግድ የአፈጻጸም ስልቱ ተለዋዋጭ በመሆኑ ድርጊቱን ለመግታትና በሀገር ኢኮኖሚ የሚያሳድረውን አሉታዊ ተጽእኖ ለመከላከል ጉምሩክ ኮሚሽን ብቻ የሚያደርገው እንቅስቃሴ በቂ ባለመሆኑ ሁሉም ባላድርሻ አካላትና ህብረተሰቡ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ የጉምሩክ ኮሚሽን ጥሪውን ያቀርባል፡፡
ጉምሩክ ኮሚሽንን የተመለከቱ ወቅታዊ፣ ትኩስ እና የተሟሉ መረጃዎችን ለማግኘት፡-
ፌስቡክ፡- https://www.facebook.com/ecczena
በድረ ገጽ፦ www.ecc.gov.et
በቴሌግራም፦ https://t.me/EthiopiaCustomsCommission